ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኵኦንን መጥቶ፦ ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፦ ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። ኢየሱስም ወደ መኵኦንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፦ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፦ የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም፦ ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት። በዚያን ጊዜ፦ እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም፦ ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም፦ እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ። ፈሪሳውያን ግን፦ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።
የማቴዎስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 9:18-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos