የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 8:1-17

የማቴዎስ ወንጌል 8:1-17 አማ54

ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። ኢየሱስም፦ እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም ለመቶ አለቃ፦ ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ፦ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ መናፍስትን በቃኣሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች