ኢየሱስ ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። በዚህ ጊዜ አንድ ለምጻም ሰው መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለ። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ለምጻሙም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፥ ከለምጹ የዳነውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ መዳንህን ለካህን አሳይ፤ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ፥ ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መባ ለእግዚአብሔር አቅርብ” አለው። ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ በገባ ጊዜ፥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ፥ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ፥ እጅግ በመሠቃየት በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ቤቴ እንድትገባ እኔ የተገባሁ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም። ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ እላችኋለሁ። የዚህ መንግሥት ወራሾች መሆን ይገባቸው የነበሩት ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ የመቶ አለቃውን “ሂድ፤ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ። ከዚያ ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስ ዐማት አተኲሶአት ታማ እንደ ተኛች አየ። እጅዋንም በዳሰሳት ጊዜ፥ ወዲያው ትኩሳቱ ለቀቃትና ዳነች፤ ተነሥታም ኢየሱስን ታገለግል ጀመር። በመሸም ጊዜ ሰዎች በአጋንንት የተያዙ ብዙ በሽተኞችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በቃሉ ርኩሳን መናፍስትን አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። ይህንንም በማድረጉ በነቢዩ ኢሳይያስ፥ “እርሱ ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ” የተባለው ትንቢት ተፈጸመ።
የማቴዎስ ወንጌል 8 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 8:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos