የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 5:1-16

የማቴዎስ ወንጌል 5:1-16 አማ54

ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች