ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም፦ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ፦ ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ፦ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ፦ ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም፦ በርባንን አሉ። ጲላጦስ፦ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም፦ ይሰቀል አሉ። ገዢውም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን፦ ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ። ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ፦ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው፦ ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥ ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው፦ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤ ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት። ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት። እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ፦ ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።
የማቴዎስ ወንጌል 27 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 27:11-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos