የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 15

15
1በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና፦ 2ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት። 3እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ? 4እግዚአብሔር፦ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ፦ አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤ 5እናንተ ግን፦ አባቱን ወይም እናቱን፦ ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥ 6አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። 7እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦
8ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥
ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
9የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል
ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።
10ሕዝቡንም ጠርቶ፦ ስሙ አስተውሉም፤ 11ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው። 12በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፦ ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት። 13እርሱ ግን መልሶ፦ የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ። 15ጴጥሮስም መልሶ፦ ምሳሌውን ተርጕምልን አለው። 16ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? 17ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? 18ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። 19ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። 20ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።
21ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። 22እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። 23እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። 24እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። 25እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። 26እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። 27እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። 28በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።
29ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። 30ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ 31ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።
32ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው። 33ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት። 34ኢየሱስም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት። 35ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ 36ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። 37ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ። 38የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። 39ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማቴዎስ ወንጌል 15