የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 8:41-56

የሉቃስ ወንጌል 8:41-56 አማ54

እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤ አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር። ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም። በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ። ኢየሱስም፦ የዳሰሰኝ ማን ነው? አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት፦ አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን? አሉ። ኢየሱስ ግን፦ አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ። ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች። እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት። እርሱም ገና ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ፦ ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም አለ። ኢየሱስ ግን ሰምቶ፦ አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች ብሎ መለሰለት። ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም። ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፦ አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ። እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት። እርሱ ግን እጅዋን ይዞ፦ አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ ብሎ ጮኸ። ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ። ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።