የሉቃስ ወንጌል 23:33-56

የሉቃስ ወንጌል 23:33-56 አማ54

ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ፦ ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው፦ አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፦ አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ፦ አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም፦ ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።