የሉቃስ ወንጌል 23:13-25

የሉቃስ ወንጌል 23:13-25 አማ54

ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ። በበዓሉ አንድ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና። ሁላቸውም በአንድነት፦ ይህን አስወግድ፥ በርባንንም ፍታልን እያሉ ጮኹ፤ እርሱም ሁከትን በከተማ አንሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወድዶ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ ነገር ግን እነርሱ፦ ስቀለው ስቀለው እያሉ ይጮኹ ነበር። ሦስተኛም፦ ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው። እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጽንተው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ። ጲላጦስም ልመናቸው እንዲሆንላቸው ፈረደበት። ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው።