ሁሉም በሞላው ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና፦ ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። ጲላጦስም፦ አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ፦ አንተ አልህ አለው። ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፦ በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። እነርሱ ግን አጽንተው፦ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ። ጲላጦስ ግን፦ ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ፦ የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፤ ከሄሮድስም ግዛት እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና። ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም። የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው ሲከሱት ቆመው ነበር። ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፥ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፥ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና።
የሉቃስ ወንጌል 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 23:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች