የሉቃስ ወንጌል 22:54-71

የሉቃስ ወንጌል 22:54-71 አማ54

ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ፦ ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። እርሱ ግን፦ አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት፦ አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ፦ እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፦ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና፦ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። ሁላቸውም፦ እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም፦ እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። እነርሱም፦ ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።