የሉቃስ ወንጌል 17:1-10

የሉቃስ ወንጌል 17:1-10 አማ54

ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው። በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ፦ ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው። ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ፦ ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ።