የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 3

3
1ቍርባኑም የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 2እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 4ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 5የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ነው። 6ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። 7ለቍርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 8እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 9ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 10ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 11ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ለእግዚአብሔር የተደረገ የቍርባን መብል ነው። 12ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 13እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 14ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 15ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 16ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የተደረገ መብል ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። 17ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ