ኦሪት ዘሌዋውያን 26:3-13

ኦሪት ዘሌዋውያን 26:3-13 አማ54

በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።