ኦሪት ዘሌዋውያን 2
2
1ማናቸውም ሰው የእህል ቁርባን ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ቁርባኑ ከመልካም ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፥ በ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ 2ወደ አሮንም ልጆች ወደ ካህናቱ ያመጣዋል፤ ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 3ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 4በእቶን የተጋገረውን የእህል ቍርባን ስታቀርብ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት የቂጣ እንጐቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። 5ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 7ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ዱቄት የተደረገ ይሁን። 8ከዚህም የተደረገውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ለካህኑም ይሰጣል፥ እርሱም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። 9ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መታሰቢያውን አንሥቶ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 11እርሾ ያለበት ነገር ማርም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት። 12እነዚህንም የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደ ጣፋጭ ሽታ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠሉም። 13የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ታጣፍጠዋለህ፤ የአምላክህንም ቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አታጐድልም፤ በቍርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ታቀርባለህ። 14ከበኵራትም የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርብ ስለዚህ ቍርባን በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ። 15ዘይትም ታፈስስበታለህ፥ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 16ካህኑም ከተፈተገው እህል ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር መታሰቢያውን ያቃጥላል፤ ይህ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ