ኦሪት ዘሌዋውያን 1
1
1እግዚአብሔርም ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ። 3መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። 4እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል። 5በሬውንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 6የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል። 7የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤ 8የአሮንም ልጆች ካህናቱ የተቈረጡትን ብልቶች ራሱንም ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤ 9የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10ቍርባኑም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል። 11በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 12በየብልቱም ራሱንም ስቡንም ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤ 13የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው። 14ለእግዚአብሔርም የሚቀርበው ቍርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቍርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል። 15ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል፥ ራሱንም ይቈለምመዋል፥ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል። ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፈጠፋል፤ 16የሆድ ዕቃውንም ከላባዎች ጋር ለይቶ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ ወገን በአመዱ ስፍራ ይጥለዋል፤ 17በክንፎቹም ይቀድደዋል፥ ነገር ግን አይከፍለውም። ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ