ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:1-36

ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:1-36 አማ54

አሌፍ። በቍጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደ ሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ። ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፥ ሰንሰለቴን አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ከለከለ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ። ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፥ ባድማ አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ። ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፥ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ። ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፥ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፥ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፦ እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፥ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች። ጤት። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ። ካፍ። ጌታ ለዘላለም አይጥልምና፥ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፥ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም። ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም።