መጽሐፈ ኢያሱ 9
9
1እንዲህም ሆነ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላማውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ 2ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ።
3የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ 4እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፥ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ። 5ያረጀ የተጠቀመም ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፥ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። 6ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች፦ ከሩቅ አገር መጥተናል፥ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን አድርጉ አሉ። 7የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያን፦ ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን? አሉአቸው። 8ኢያሱንም፦ እኛ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ኢያሱም፦ እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ? አላቸው። 9እነርሱም አሉት፦ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባሪያዎችህ መጥተናል፥ ዝናውንም፥ በግብፅም ያደረገውን ሁሉ፥ 10በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ፦ ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ፦ እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፥ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን። 12ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፥ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም። 13እነዚህም የጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፥ እነሆም፥ ተቀድደዋል፥ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል። 14ሰዎቹም ከስንቃቸው ወሰዱ፥ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም። 15ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፥ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።
16ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ በመካከላቸውም እንደ ኖሩ ሰሙ። 17የእስራኤልም ልጆች ተጉዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው መጡ፥ የከተሞቻቸውም ስም ገባዖን፥ ከፊራ፥ ብኤሮት፥ ቂርያትይዓሪም ነበረ። 18የሕዝቡም አለቆች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በአለቆቹ ላይ አጉረመረሙ። 19አለቆቹም ሁሉ ለማኅበሩ ሁሉ፦ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ምለንላቸዋል፥ ስለዚህም እንነካቸው ዘንድ አይገባንም። 20ስለ ማልንላቸው መሓላ ቁጣ እንዳይወርድብን ይህን እናድርግባቸው፥ በሕይወትም እንተዋቸው አሉአቸው። 21አለቆቹም፦ በሕይወት ይኑሩ አሉአቸው፥ አለቆቹም እንደ ተናገሩአቸው ለማኅበሩ ሁሉ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች ሆኑ።
22ኢያሱም ጠርቶ፦ እናንተ በመካከላችን ስትኖሩ፦ ከእናንተ እጅግ የራቅን ነን ብላችሁ ለምን አታለላችሁን? 23አሁንም የተረገማችሁ ናችሁ፥ ለአምላኬም ቤት እንጨት ቈራጭ ውኃም ቀጂ የሆነ ባሪያ ከእናንተ ለዘላለም አይጠፋም አላቸው። 24መልሰውም ኢያሱን፦ እኛ ባሪያዎችህ ምድሪቱን ሁሉ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ ያጠፋ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፥ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን፥ ይህንንም ነገር አድርገናል። 25አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ውስጥ ነን፥ ለዓይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን አሉት። 26እንዲሁም አደረገባቸው፥ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፥ አልገደሉአቸውምም። 27በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠውም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቈራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ