የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 8

8
1እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ሰልፈኞችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፥ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። 2በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፥ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፥ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ አለው።
3ኢያሱም ሰልፈኞቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፥ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ 4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፥ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ተዘጋጁ፥ 5እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፥ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፥ 6አስቀድመን እንደ ሸሸን የምንሸሽ ይመስላቸዋልና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፥ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። 7እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። 8በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጉ፥ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ። 9ኢያሱም ሰደዳቸው፥ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፥ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ።
10ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ ሕዝቡንም አሰለፈ፥ እርሱም የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። 11ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፥ ወደ ከተማይቱም ፊት ደረሱ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፥ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። 12አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው። 13በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የተደበቁትን ሕዝብ አኖሩ፥ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ። 14የጋይም ንጉሥ ባየ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ቸኩለው በማለዳ ተነሡ፥ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በሰልፍ ለመገናኘት ወጡ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር። 15ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ። 16በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሊያሳድዱአቸው ተጠሩ፥ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። 17በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፥ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት።
18እግዚአብሔር ኢያሱን፦ ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ አለው፥ ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ። 19የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፥ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት። 20የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፥ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም፥ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ። 21ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ እንደ ተነሣ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ። 22ሌሎቹም በላያቸው ከከተማይቱ ወጡ፥ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፥ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው። 23የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።
24እንዲህም ሆነ፥ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከወደቁ በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት። 25በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ አሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ። 26ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስከሚያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ኢያሱን እንዳዘዘው ቃል የዚያችን ከተማ ከብትና ምርኮ እስራኤል ለራሳቸው ዘረፉ። 28ኢያሱም ጋይን አቃጠላት፥ እስከ ዛሬም ድረስ ድብድባና በረሃ ለዘላለም አደረጋት። 29የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው፥ ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ሬሳውንም ከዛፍ አወረዱት፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ጣሉት፥ በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት።
30የዚያን ጊዜም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። 31የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዘ፥ በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፥ መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ፥ በእርሱም ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት ሠዉ። 32የእስራኤልም ልጆች ሲያዩ በዚያ ስፍራ በድንጋዮቹ ላይ የሙሴን ሕግ ጻፈባቸው። 33የእስራኤልንም ሕዝብ አስቀድሞ ይባርኩ ዘንድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘ፥ እስራኤል ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ፈራጆቻቸውም፥ የአገሩ ልጆችም፥ መጻተኞችም፥ እኩሌቶቹ በገሪዛን ተራራ ፊት እኩሌቶቹም በጌባል ተራራ ፊት ሆነው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፥ በታቦቱም ፊት በወዲህና በወዲያ ቆመው ነበር። 34ከዚህም በኋላ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፥ የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ። 35ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሁሉን አነበበ እንጂ ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል አላስቀረም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ