የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አላቸው። ሕዝቡንም፦ ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ሰልፈኞችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አለ። ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፥ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፥ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ። ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፥ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፥ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፥ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፥ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ፦ እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፥ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፥ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፥ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ። ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፥ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
መጽሐፈ ኢያሱ 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 6:6-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos