ኢያሱም ካህናቱን ጠርቶ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ከእናንተም ሰባታችሁ እምቢልታ ይዛችሁ ከታቦቱ ፊት ቅደሙ።” ሕዝቡንም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “ሂዱ፤ ከተማይቱን ዙሩ፤ ወታደሮቹም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ”። ኢያሱ ሕዝቡን ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ቀንደ መለከቱን እየነፉ ወደፊት ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ተከተላቸው። ወታደሮቹም ቀንደ እምቢልታ ከሚነፉት ካህናት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱ እምቢልታውን ሳያቋርጡ እየነፉ ሕዝቡ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። ኢያሱ ግን፦ “ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ እንዳትጮኹ፤ ወይም ድምፃችሁ እንዳይሰማ፤ እንዲያውም አንዲት ቃል እንኳ እንዳትናገሩ፤ ጩኹ ስላችሁ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ” ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። በዚህ ዐይነት የእግዚአብሔር ታቦት ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ፥ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ በዚያ ዐዳር ሆነ። በማግስቱ ኢያሱ በማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱን እምቢልታ የያዙት ሰባት ካህናት እምቢልታቸውን ሳያቋርጡ እየነፉ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ለፊት ሄዱ፤ መለከቱ ሳያቋርጥ እየተነፋ ወታደሮቹ ከካህናቱ ቀድመው ሌላው ሕዝብ ደግሞ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። በዚህም በሁለተኛው ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ እስከ ስድስት ቀንም በዚሁ ዐይነት አደረጉ። በሰባተኛው ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሥተው በዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፤ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩበት ቀን ይህ ብቻ ነበር። በሰባተኛው ዙር ካህናቱ እምቢልታ ሊነፉ በሚዘጋጁበት ጊዜ ኢያሱ ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ከተማይቱን ስለ ሰጣችሁ ጩኹ!” ብሎ አዘዘ። “በከተማይቱና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተረገመ ሆኖ መደምሰስ አለበት፤ ሴትኛ ዐዳሪዋ ግን የላክናቸውን ሰላዮች ደብቃ ስላዳነች መትረፍ የሚገባቸው እርስዋና ከእርስዋ ጋር በቤትዋ ያሉት ብቻ ናቸው። እናንተ ግን በእስራኤል ሰፈር ችግርንና ጥፋትን እንዳታስከትሉ መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች ማናቸውንም ጓጒታችሁ ከመውሰድ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ብርና ወርቅ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን፤ እርሱም በእግዚአብሔር የዕቃ ግምጃ ቤት መቀመጥ አለበት።” ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤ ሰይፋቸውንም መዘው በከተማይቱ የተገኘውን ወንዱንም ሴቱንም ወጣቱንና ሽማግሌውን ሁሉ ገደሉ፤ የከብት፥ የበግና የአህያውን መንጋ ሁሉ ፈጁ።
መጽሐፈ ኢያሱ 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 6:6-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos