የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 3:7-17

መጽሐፈ ኢያሱ 3:7-17 አማ54

እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ሁሉ ዓይን ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ። አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት፦ በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ አለው። ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፦ ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አለ። ኢያሱም አለ፦ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈፅሞ እንዲያወጣ በዚህ ታውቃላችሁ። እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል። አሁንም ከእስራኤል ነገዶች አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጡ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን። እንዲህም ይሆናል፥ የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል፥ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል። እንዲህም ሆነ፥ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፥ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፥ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፥ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፥ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳንስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ።