እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትንም ካህናት፣ ‘ከዮርዳኖስ ውሃ ዳር ስትደርሱ፣ በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ’ በላቸው።” ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ “ወደዚህ ቀርባችሁ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አላቸው፤ እንግዲህ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ መሆኑንና እርሱም በርግጥ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ኤዊያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ እንዴት አድርጎ እንደሚያሳድዳቸው የምታውቁት በዚህ ነው። እነሆ፤ የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት ቀድሟችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል። እንግዲህ ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጡ፤ ከየነገዱም አንዳንድ ሰው ይሁን። የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ገና እግራቸውን በዮርዳኖስ ውሃ ውስጥ እንዳስገቡ፣ ቍልቍል የሚወርደው ውሃ ወዲያውኑ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።” ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ሰፈሩን ለቀው ሲወጡ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከፊታቸው ቀድመው ሄዱ። ወቅቱም የመከር ጊዜ በመሆኑ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ነበር፤ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ “አዳም” ተብላ እስከምትጠራው ሩቅ ከተማ ድረስ በመከማቸት እንደ ክምር ተቈለለ፤ ቍልቍል ወደ ዓረባ ጨው ባሕር የሚወርደውም ውሃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም ከኢያሪኮ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ተሻገሩ። የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናትም፣ ሕዝቡ ሁሉ፣ ማለት እስራኤል በሙሉ ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቁ ምድር ላይ ቀጥ ብለው ቆመው ነበር።
ኢያሱ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢያሱ 3
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢያሱ 3:7-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos