ትንቢተ ኢዩኤል 3
3
1እነሆም፥ በዚያ ወራትና በዚያ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ 2አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፥ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን ምድሬንም የተካፈሉአትን እፋረድባቸዋለሁ። 3በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሸጡ፥ ጠጡም።
4ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ብድራትን ብትመልሱልኝ ፈጥኜ በችኰላ ብድራታችሁን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። 5ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥ 6ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ 7እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። 8እግዚአብሔር ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል።
9ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ፥ ለሰልፍ ተዘጋጁ፥ ኃያላንን አስነሡ፥ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። 10ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፥ ደካማውም፦ እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። 11እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸኵላችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። 12አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፥ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። 13መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፥ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፥ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል።
14የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። 15ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። 16እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፥ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፥ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። 17እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም።
18በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፥ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። 19በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። 20ነገር ግን ይሁዳ ለዘላለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። 21እኔም ንጹሕ ያላደረግሁትን ደማቸውን ንጹሕ አደርገዋለሁ፥ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢዩኤል 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ