መጽሐፈ ኢዮብ 36
36
1ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ፦
2ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና
ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ።
3እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥
ፈጣሪዬንም፦ ጻድቅ ነው እላለሁ።
4ቃሌ በእውነት ያለ ሐሰት ነው፥
በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ።
5እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፥
እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው።
6እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፥
ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል።
7ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፥
ለዘላለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥
እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።
8በሰንሰለት ቢታሰሩ፥
ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥
9ሥራቸውንና መተላለፋቸውን
በትዕቢትም እንዳደረጉ ይናገራቸዋል።
10ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥
ከኃጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።
11ቢሰሙ ቢያገለግሉትም፥
ዕድሜአቸውን በልማት፥
ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።
12ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥
ያለ እውቀትም ይሞታሉ።
13ዝንጉዎች ግን ቍጣን ያዘጋጃሉ፥
እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም።
14በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥
ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል።
15የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፥
በመከራም ጆሮአቸውን ይገልጣል።
16እንዲሁም አንተን ከመከራ
ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥
በማዕድህ ላይ የተዘጋጀውም ስብ በሞላበት ነበር።
17አንተ ግን በበደለኞች ፍርድ የተሞላህ ነህ፥
ስለዚህ ፍርድና ብይን ይይዝሃል።
18ቍጣ ለስድብ አያታልልህ፥
የማማለጃም ብዛት ፈቀቅ አያድርግህ።
19ባለጠግነትህ የኃይልህም ብርታት ሁሉ
ያለ ችግር እንድትሆን ሊረዳህ ይችላልን?
20ወገኖች ከስፍራቸው የሚወጡበትን ሌሊት አትመኝ።
21ከመከራ ይልቅ ይህን መርጠሃልና
ኃጢአትን እንዳትመለከት ተጠንቀቅ።
22እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፥
እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?
23መንገዱን ማን አዘዘለት?
ወይስ፦ ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው?
24ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ።
25ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፥
ሰውም ከሩቅ ያየዋል።
26እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም።
የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።
27የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥
ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፥
28ደመናት ያዘንባሉ፥
በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ።
29የደመናውንም መዘርጋት፥
የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው?
30እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፥
የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል።
31በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፥
ብዙም ምግብ ይሰጣል።
32እጆቹን በብርሃን ይሰውራል፥
በጠላቱም ላይ ይወጣ ዘንድ ያዝዘዋል፥
33የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፥
እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 36: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ