መጽሐፈ ኢዮብ 28
28
1በእውነት ብር የሚወጣበት፥
ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፥
መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል።
3ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፥
የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል።
4ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ
ከሰውም እግር ተረሱ፥
ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ።
5እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፥
በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል።
6ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥
የወርቅም ድቃቂ አለው።
7መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥
የአሞራም ዓይን አላየውም።
8የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥
ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።
9ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥
ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል።
10ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፥
ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች።
11ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፥
የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።
12ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው?
የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
13ሰው መንገድዋን አያውቅም፥
በሕያዋን ምድር አትገኝም።
14ቀላይ፦ በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፥
ባሕርም፦ በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።
15በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥
ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም።
16በኦፊር ወርቅ፥
በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥
በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም።
18ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም።
የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል።
19የኢትዮጵያ ቶጳዝዩን አይተካከላትም፥
በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
20እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች?
የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
21ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥
ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች።
22ጥፋትና ሞት፦ ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።
23እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥
እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።
24እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥
ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥
ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥
26ለዝናብም ሥርዓትን፥
ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥
27በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፥
አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት።
28ሰውንም፦ እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፥
ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 28: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ