መጽሐፈ ኢዮብ 26
26
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው!
ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው!
3ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው!
ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት!
4ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ?
የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ?
5ሙታን ሰዎች ከውኆች በታች፥
በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ በታች ይንቀጠቀጣሉ።
6ሲኦል በፊቱ ራቁትዋን ናት፥
ለጥፋትም መጋረጃ የለውም።
7ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥
ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል።
8ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፥
ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም።
9የዙፋኑን ፊት ይከድናል፥
ደመናውንም ይዘረጋበታል።
10ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥
በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አደረገ።
11የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥
ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ።
12በኃይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥
በማስተዋሉም ረዓብን ይመታል።
13በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥
እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች።
14እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፥
ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው!
የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 26: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ