መጽሐፈ ኢዮብ 16
16
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፥
እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
3በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን?
ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
4እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፥
ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥
እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥
ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
5በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፥
የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።
6እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፥
ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም።
7አሁን ግን አድክሞኛል፥
ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል።
8መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፥
ክሳቴም ተነሥቶብኛል፥
በፊቴም ይመሰክርብኛል።
9በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፥
ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፥
ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፥
10እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፥
እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፥
በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ።
11እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥
በክፋዎችም እጅ ጣለኝ።
12ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፥
አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፥
እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ።
13ቀስተኞቹ ከበቡኝ፥
ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፥
ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ።
14በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፥
እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል።
15በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥
ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ።
16ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፥
የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፥
17ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፥
ጸሎቴም ንጹሕ ነው።
18ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥
ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን።
19አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥
የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው።
20ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥
ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ።
21የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥
ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ!
22ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላ
እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 16: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ