የዮሐንስ ወንጌል 9:24-41

የዮሐንስ ወንጌል 9:24-41 አማ54

ስለዚህ ዕውር የነበረው ሰው ሁለተኛ ጠርተው፦ “እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም መልሶ፦ “ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ” አለ። ደግመውም፦ “ምን አደረገህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ?” አሉት። እርሱም መልሶ፦ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን?” አላቸው። ተሳድበውም፦ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም” አሉት። ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው፦ “ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።” መልሰው፦ “አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወልድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ያገኘውም፦ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ፦ “ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም፦ “አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፦ “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ” አለ። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው፦ “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው፦ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን፦ ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።