የዮሐንስ ወንጌል 18:1-14

የዮሐንስ ወንጌል 18:1-14 አማ54

ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እነርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። ኢየሱስ፦ “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ፦ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ደግሞም፦ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፦ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ “እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ ይህም፦ “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው። እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥ አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። ቀያፋም፦ “አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል” ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ።