የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 16:5-16

የዮሐንስ ወንጌል 16:5-16 አማ54

አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም፦ “ወዴት ትሄዳለህ?” ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ከእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል” አልሁ። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።”