ትንቢተ ኤርምያስ 48
48
1ስለ ሞዓብ፥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ናባው ጠፍታለችና ወዮላት! ቂርያታይም አፍራለች ተይዛማለች፥ ሚሥጋብ አፍራለች ደንግጣማለች። 2ከእንግዲህ ወዲህ የሞዓብ ትምክሕት የለም፥ በሐሴቦን ላይ፦ ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት ብለው ክፉ ነገር አስበውባታል። መድሜን ሆይ፥ አንቺ ደግሞ ትጠፊአለሽ ሰይፍም ያሳድድሻል። 3መፍረስና ታላቅ ጥፋት የሚል የጩኸት ቃል ከሖሮናይም ተሰማ። 4ሞዓብ ጠፍታለች፥ ልጆችዋም ጩኸትን አሰምተዋል። 5በሉሒት ዓቀበት ልቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉና፥ በሖሮናይምም ቍልቍለት የጥፋትንና የመባባትን ጩኸት ሰምተዋል። 6ሸሽታችሁ ራሳችሁን አድኑ፥ በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ሁኑ። 7በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፥ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል። 8እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ አጥፊ ወደ ከተማ ሁሉ ይመጣል አንዲትም ከተማ አትድንም፥ ሸለቆውም ይጠፋል ሜዳውም ይበላሻል። 9በርራ እንድትወጣ ለሞዓብ ክንፍ ስጡአት፥ ከተሞችዋም ባድማና ወና ይሆናሉ። 10የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፥ ሰይፉንም ከደም የሚከለክል ርጉም ይሁን።
11ሞዓብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ቅምጥል ነበረ፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃውም ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፥ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። 12ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሚያገላብጡትን የምልክበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ያገላብጡታል፥ ጋኖቹንም ባዶ ያደርጋሉ፥ መስቴዎቹንም ይሰብራሉ። 13የእስራኤልም ቤት ይታመንባት ከነበረው ከቤቴል እንዳፈረ፥ እንዲሁ ሞዓብ ከካሞሽ ያፍራል። 14እናንተ፦ እኛ ኃያላን በሰልፍም ጽኑዓን ነን እንዴት ትላላችሁ? 15ሞዓብ ፈርሶአል፥ ከተሞቹም ጠፍተዋል፥ የተመረጡትም ጕልማሶች ወደ መታረድ ወርደዋል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ ንጉሥ። 16የሞዓብ ጥፋት ሊመጣ ቀርቦአል መከራውም እጅግ ይፈጥናል። 17በዙሪያው ያላችሁ ሁሉ ስሙንም የምታውቁ ሁሉ፦ ብርቱው በትር፥ የከበረው ሽመል፥ እንዴት ተሰበረ! ብላችሁ አልቅሱለት። 18በዲቦን የምትኖሪ ሆይ፥ ሞዓብን የሚያጠፋ ወጥቶብሻልና፥ አምባሽንም ሰብሮአልና ከክብርሽ ውረጂ በጥማትም ተቀመጪ። 19በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፥ በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፥ የሸሸውንና ያመለጠችውን፦ ምን ሆኖአል? ብለሽ ጠይቂ። 20ሞዓብም ፈርሶአልና አፈረ፥ አልቅሱ ጩኹም፥ ሞዓብ እንደ ተዘረፈ በአርኖን አጠገብ አውሩ። 21በሜዳ ላይ፥ በሖሎን፥ በያሳ፥ በሜፍዓት ላይ፥ 22በዲቦን፥ በናባው፥ በቤት ዲብላታይም ላይ፥ 23በቂርያታይም፥ በቤትጋሙል፥ 24በቤትምዖን ላይ፥ በቂርዮት፥ በባሶራ፥ በሞዓብም ምድር ከተሞች ሁሉ ቅርብና ሩቅ በሆኑ ላይ ፍርድ መጥቶአል። 25የሞዓብ ቀንድ ተቈረጠ ክንዱም ተሰበረ፥ ይላል እግዚአብሔር።
26በእግዚአብሔር ላይ ኰርቶአልና አስክሩት፥ ሞዓብም በጥፋቱ ላይ ይንከባለላል፥ ደግሞም መሳቂያ ይሆናል። 27እስራኤል ለአንተ መሳቂያ አልሆነምን? ወይስ በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን? ስለ እርሱ በተናገርህ ጊዜ ራስህን ትነቀንቃለህ። 28እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፥ ከተሞችን ትታችሁ በዓለት ውስጥ ተቀመጡ፥ በገደል አፋፍም ቤትዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ ሁኑ። 29እጅግ እንደ ታበየ ስለ ሞዓብ ትዕቢት ስለ ትምክህቱም ስለ ኵራቱም ስለ መጓደዱም ስለ ልቡም ትዕቢት ሰምተናል። 30ቍጣው ምንም እንደ ሆነ አውቃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፉከራው ምንም አልሠራም። 31ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ ለሞዓብም ሁሉ እጮኻለሁ፥ ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ። 32አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ፥ ከኢያዜር ልቅሶ ይልቅ ለአንቺ አለቅሳለሁ፥ ቅርንጫፎችሽ ባሕርን ተሻግረዋል፥ ወደ ኢያዜርም ባሕር ደርሰዋል፥ አጥፊው በሰብልሽና በወይንሽ ላይ መጥቶአል። 33ሐሤትና ደስታ ከፍሬያማው እርሻና ከሞዓብ ምድር ጠፍተዋል፥ ጠጁን ከመጥመቂያው አጥፍቻለሁ፥ ጠማቂውም በእልልታ አይጠምቅም፥ እልልታቸውም እልልታ አይሆንም። 34ከሐሴቦን ጩኸት እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ ድረስ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፥ ከዞዓር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ይደርሳል፥ የኔምሬም ውኃ ደግሞ ይደርቃል። 35በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን ለአማልክቱም የሚያጥነውን ከሞዓብ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
36ያተረፈው ትርፉ ጠፍቶበታልና፥ ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ እንቢልታ ይጮኻል፥ ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ይጮኻል። 37ራስ ሁሉ መላጣ ጢምም ሁሉ የተላጨ ነውና፥ በእጅም ሁሉ ላይ ክትፋት በወገብም ላይ ማቅ አለና። 38ሞዓብን እንደማይወደድ ዕቃ ሰብሬአለሁና በሞዓብ ሰገነት ሁሉ ላይ በአደባባዩም ላይ በሁሉም ቦታ ልቅሶ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 39እንዴት ተገለበጠ! በእፍረትም የተነሣ ሞዓብ ጀርባውን እንዴት መለሰ! ብላችሁ አልቅሱ። ሞዓብም በዙሪያው ላሉት ሁሉ መሳቂያና ድንጋጤ ይሆናል።
40እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እንደ ንስር ይበርራል ክንፉንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል። 41ከተሞቹ ተይዘዋል፥ አምባዎቹም ተወስደዋል፥ በዚያም ቀን የሞዓብ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል። 42ሞዓብም በእግዚአብሔር ላይ ኰርቶአልና ሕዝብ ከመሆን ይጠፋል። 43በሞዓብ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ጕድጓድ ወጥመድም በአንተ ላይ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 44በሞዓብ ላይ የመጐብኘትን ዓመት አመጣበታለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍርሃት የሸሸ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቃል፥ ከጕድጓድም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 45የሸሹ ደክመው ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፥ እሳት ከሐሴቦን ነበልባልም ከሴዎን ወጥቶአል የሞዓብንም ማዕዘን የሤትንም ልጆች አናት በልቶአል። 46ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የካሞሽ ወገን ጠፍቶአል፥ ወንዶች ልጆችህ ተማርከዋልና፥ ሴቶች ልጆችህም ወደ ምርኮ ሄደዋልና። 47ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። የሞዓብ ፍርድ እስከዚህ ድረስ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 48: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ