ትንቢተ ኤርምያስ 36
36
1እንዲህም ሆነ፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 3ምናልባት የይሁዳ ቤት፦ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ።
4ኤርምያስም የኔርያን ልጀ ባሮክን ጠራ፥ ባሮክም እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። 5ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ እኔ ተግዤአለሁ፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እገባ ዘንድ አልችልም። 6አንተ ግን ሂድ፥ ከአፌም የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆር በክርታሱ አንብብ፥ ደግሞም ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። 7እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ጸሎታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትወድቅ ይሆናል፥ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል። 8የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ።
9እንዲህም ሆነ፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ። 10ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ጓዳ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ በመጽሐፉ አነበበ።
11የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ በሰማ ጊዜ፥ 12ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ጓዳ ወረደ፥ እነሆም፥ አለቆች ሁሉ፥ ጸሐፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 13ሚክያስም ባሮክ በሕዝቡ ጆሮ በመጽሐፉ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 14አለቆቹም ሁሉ፦ በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና የሚል መልእክት በኵሲ ልጅ በሰሌምያ ልጅ በናታንያ ልጅ በይሁዲ እጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ መጣ። 15እነርሱም፦ እስኪ ተቀመጥ፥ በጆሮአችንም አንብብ አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው። 16ቃሉንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተመካከሩ፥ ባሮክንም፦ ይህን ቃል ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን አሉት። 17ባሮክንም፦ ይህን ቃል ሁሉ ከአፉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን ብለው ጠየቁት። 18ባሮክም፦ ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፥ እኔም በመጽሐፉ ላይ በቀለም እጽፍ ነበር ብሎ መለሰላቸው። 19አለቆቹም ባሮክን፦ አንተና ኤርምያስ ሂዱ፥ ተሸሸጉ፥ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ አሉት።
20ወደ ንጉሡም ወደ አደባባይ ገቡ፥ ክርታሱንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ጓዳ አኑረውት ነበር፥ ቃሉንም ሁሉ በንጉሡ ጆሮ ተናገሩ። 21ንጉሡም ክርታሱን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከ፥ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ጓዳ ወሰደው፥ ይሁዲም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። 22ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር። 23ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያህል ባነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ በካራ ቀደደው፥ ክርታሱም በምድጃ ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ጣለው። 24ንጉሡም ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም። 25ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም። 26ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፥ እግዚአብሔር ግን ሰወራቸው።
27ንጉሡም ክርስታሱንና ባሮክ ከኤርምያስ አፍ የጻፈውን ቃል ካቃጠለ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 28ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 29የይሁዳንም ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ፦ የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። 30ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀማጭ አይኖርለትም፥ ሬሳውም በቀን ለትኩሳት በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። 31ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን ባሪያዎቹንም እቀጣለሁ፥ እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።
32ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው፥ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ጻፈበት፥ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 36: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ