ትንቢተ ኤርምያስ 35
35
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፦ 2ወደ ሬካባውያን ቤት ሄደህ ተናገራቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዲቱ አግባቸው የወይን ጠጅም አጠጣቸው። 3የከባስንን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን ወንድሞቹንም ልጆቹንም ሁሉ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኋቸው፥ 4ወደ እግዚአብሔርም ቤት በበረኛው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አገባኋቸው። 5በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ፦ የወይኑን ጠጅ ጠጡ አልኋቸው። 6እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፦ የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና፦ እናንተና ልጆቻችሁ ለዘላለም የወይን ጠጅ አትጠጡ። 7በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንም አትትከሉ፥ አንዳችም አይሁንላችሁ። 8እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፥ እኛም ሚስቶቻችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፥ 9የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፥ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፥ 10በድንኳንም ውስጥ ተቀምጠናል፥ ታዝዘናል፥ አባታችንም ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል። 11ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ፦ ኑ ከከለዳውያን ሠራዊትና ከሶርያ ሠራዊት ፊት የተነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ አልን፥ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።
12የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር። 14የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃል ተፈጸመ፥ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፥ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናግሬአችኋለሁ፥ ተናገርሁ፥ ሆኖም አልሰማችሁኝም። 15ደግሞም፦ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ታመልኩአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፥ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም። 16የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋልና፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝምና 17ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።
18ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም ፈጽማችኋልና፥ 19ስለዚህ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘላለም አይታጣም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 35: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ