ትንቢተ ኤርምያስ 33:14-26

ትንቢተ ኤርምያስ 33:14-26 አማ54

እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፥ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፥ የምትጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቍጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ይህ ሕዝብ፦ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፥ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።