የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 33:1-26

ትንቢተ ኤርምያስ 33:1-26 አማ54

ኤርምያስ ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣለት፦ ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፥ ያደረገው እግዚአብሔር፥ ያጸናውም ዘንድ የሠራው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፥ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለአፈር ድልድልና ለምሽግ ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፥ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች እንዲህ ይላልና፦ ከለዳውያን ለመዋጋት መጥተዋል፥ ነገር ግን በቍጣዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሉአቸው ነው፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ሰውሬአለሁና። እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸውማለሁ፥ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ። የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ። እኔንም ከበደሉበት ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ እኔንም የበደሉኝን ያመፁብኝንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ። ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ እኔም ስላመጣሁላቸው በጎነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ ስም ለምስጋናም ለክብርም ትሆናለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት በምትሉአት በዚህች ስፍራ፥ የሚቀመጥባቸው በሌላ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ፥ የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡት ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የምድርን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ባድማ ሆኖ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባለው በዚህ ስፍራ በከተሞችም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉት የእረኞች መኖሪያ ይሆናል። በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች መንጎቹ በተቈጣጣሪው እጅ እንደ ገና ያልፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፥ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፥ የምትጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። የሰማይን ሠራዊት መቍጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ ይህ ሕዝብ፦ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፥ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።