የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 33:1-26

ኤርምያስ 33:1-26 NASV

ኤርምያስ በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ በግዞት ሳለ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እርሱ መጣ፤ “ምድርን የፈጠራት፣ ያበጃትና የመሠረታት እግዚአብሔር፣ ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፣ እርሱ እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ።’ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከባቢሎናውያን ጋር ባለው ውጊያ፣ ዐፈር በመደልደልና በሰይፍ የሚደረገውን ጥቃት ለመከላከል ስለ ፈረሱት ስለዚህች ከተማ ቤቶችና ስለ ይሁዳ ነገሥታት ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤ ‘እነዚህ በቍጣዬና በመዓቴ በምገድላቸው ሰዎች ሬሳ ይሞላሉ፤ ስለ ክፋቷ ሁሉ ከዚህች ከተማ ፊቴን እሰውራለሁ። “ ‘ይሁን እንጂ፣ ፈውስንና ጤንነትን እንደ ገና እሰጣታለሁ፤ ሕዝቤንም እፈውሳለሁ፤ በብዙ ሰላምና በርጋታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ። የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ቀድሞ እንደ ነበሩት ሁኔታ አድርጌ አበጃቸዋለሁ፤ እኔን ከበደሉበት ኀጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ፤ በእኔ ላይ ያመፁበትንም ኀጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ። ይህች ከተማ፣ ለእርሷ ያደረግሁትን በጎ ነገር ሁሉ በሚሰሙት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ለዝና፣ ለደስታ፣ ለምስጋናና ለክብር ትሆናለች፤ ከምሰጣትም የተትረፈረፈ ብልጽግናና ሰላም የተነሣ ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም።’ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህችን ስፍራ፣ “ሰውና እንስሳት የማይኖሩባት ባድማ ናት” ትላላችሁ፤ ነገር ግን ሰውም ሆነ እንስሳ ባልነበሩባቸውና ባድማ በሆኑት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች፣ እንደ ገና ድምፅ ይሰማል፤ የሐሤትና የደስታ ድምፅ፣ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ እንዲሁም፣ “ ‘ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚል የምስጋናን መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ሰዎች ድምፅ ይሰማል፤ የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ እመልሳለሁና፤’ ይላል እግዚአብሔር። “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰውም ሆነ እንስሳት በማይኖሩበት በዚህ ባዶ ስፍራ፣ በከተማዎቹም ሁሉ እረኞች መንጎቻቸውን የሚያሳርፉበት እንደ ገና ያገኛሉ። በተራራማው አገር፣ በምዕራብ ተራሮች ግርጌና በኔጌብ ባሉ ከተሞች በብንያም አገር፣ በይሁዳ ከተሞች እንዲሁም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች መንጎች እንደ ገና በሚቈጥራቸው ሰው እጅ ሥር ያልፋሉ’ ይላል እግዚአብሔር። “ ‘ለእስራኤል ቤትና ለይሁዳ ቤት የገባሁትን የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር። “ ‘በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ፤ በምድሪቱም ፍትሕንና ጽድቅን ያደርጋል። በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም በሰላም ትኖራለች፤ የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤ ሌዋውያን ከሆኑት ካህናትም የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእህል ቍርባን ለማቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ለመሠዋት ሁልጊዜ በፊቴ የሚቆም ሰው አይታጣም።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለቀንና ለሌሊት የወሰንሁትን ሥርዐት በማፋለስ ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዳይፈራረቁ ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፣ በዚያ ጊዜ ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር የገባሁትን ኪዳን፣ እንዲሁም በፊቴ በክህነት ከሚያገለግሉት ሌዋውያን ጋር የገባሁትን ኪዳን ማፍረስ ይቻላል፤ ዳዊትም ከእንግዲህ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ዘር አይኖረውም። የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እንዲሁም በፊቴ የሚቆሙትን ሌዋውያን እንደማይቈጠሩ እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደማይሰፈር የባሕር አሸዋ አበዛቸዋለሁ።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን መንግሥታት ጥሏል’ እንደሚሉ አላስተዋልህምን? ሕዝቤን ንቀዋል፤ እንደ ሕዝብም አልቈጠሯቸውም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀንና የሌሊት ኪዳኔን፣ የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት ያጸናሁ እኔ ካልሆንሁ፣ የያዕቆብንና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ከልጆቹም በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ ዘር ላይ ገዥ እንዲሆኑ አልመርጥም፤ ይህንም የምለው ምርኳቸውን ስለምመልስና ስለምራራላቸው ነው።’ ”