የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 28

28
1በዚያም ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 2የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይናገራል፦ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። 3የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳትን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳታለሁ፥ 4ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።
5ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ። 6ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፦ አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፥ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም። 7ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፥ 8ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። 9ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።
10ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። 11ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ አለ። ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ።
12ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ። 14የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፥ እነርሱም ይገዙለታል፥ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 15ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን፦ ሐናንያ ሆይ፥ ስማ፥ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ እግዚአብሔር አልላከህም። 16ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከምድር ላይ እሰድድሃለሁ፥ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ አለው። 17ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ