ትንቢተ ኤርምያስ 20:7-14

ትንቢተ ኤርምያስ 20:7-14 አማ54

አቤቱ፥ አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፥ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል። በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፥ ግፍና ጥፋት ብዬ እጮኻለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና ዋዛ ሆኖብኛልና። እኔም፦ የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፥ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም። የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ፦ ምናልባት ይታለል እንደ ሆነ፥ እናሸንፈውም እንደ ሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደ ሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን ይላሉ። እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ ጨካኝ ከእኔ ጋር ነው፥ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፥ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘላለምም በማይረሳ ጕስቍልና ይጐሰቍላሉ። አቤቱ፥ ጻድቅን የምትመረምር ኵላሊትንና ልብን የምትመለከት የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ለይ። ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔርንም አመስግኑ፥ የችግረኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና። የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን፥ እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን።