ትንቢተ ኤርምያስ 17
17
1የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፥ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ተቀርጾአል። 2ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና የማምለኪያ ዐፀዳቸውን ያስባሉ። 3በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ። 4አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ ለዘላለምም በማታውቃትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርግሃለሁ፥ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። 6በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፥ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። 7በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። 8በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።
9የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፥ ማንስ ያውቀዋል? 10እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ። 11ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ እንዲሁ በቅን ሳይሆን ባለጠግነትን የሚሰበስብ ሰው ነው፥ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።
12የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። 13አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ። 14አቤቱ፥ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፥ አድነኝ እኔም እድናለሁ፥ አንተ ምስጋናዬ ነህና። 15እነሆ፦ የእግዚአብሔር ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ ይሉኛል። 16እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፥ አንተ ታውቃለህ፥ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ። 17ለማስፈራራት አትሁንብኝ፥ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ። 18አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፥ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፥ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።
19እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፥ 20እንዲህም በላቸው፦ በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፥ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥ 22ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፥ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ። 23እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ።
24እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥ 25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፥ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። 26የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ። 27ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ