ትንቢተ ኤርምያስ 16
16
1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይሁኑልህ። 3እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና፦ 4በክፉ ሞት ይሞታሉ፥ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፥ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ።
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰላሜን፥ ቸርነትና ምሕረትን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ታለቅስም ታዝንም ዘንድ አትሂድ። 6ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፥ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም ስለ እነርሱም ገላን አይነጩላቸውም ራስንም አይላጩላቸውም፥ 7ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። 8ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። 9የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
10ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፦ ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገርን ስለ ምን እግዚአብሔር ተናገረብን? በደላችንስ ምንድር ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድር ነው? ቢሉህ፥ 11አንተ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም፥ እነርሱም ትተውኛል፥ ሕጌንም አልጠበቁም፥ 12እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፥ እነሆም፥ ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ እልከኝነት ሄዳችኋል እኔንም አልሰማችሁም። 13ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፥ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ።
14ስለዚህ፥ እነሆ፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ 15ነገር ግን፦ የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፥ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
16እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰድዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፥ ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰድዳለሁ፥ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድኑአቸዋል። 17ዓይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፥ ከፊቴም አልተሰወሩም፥ ኃጢአታቸውም ከዓይኔ አልተሸሸገም። 18ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።
19አቤቱ፥ ኃይሌ፥ አምባዬ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ሆይ፥ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው፦ በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር የማይረባቸውንም ወርሰዋል ይላሉ። 20በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክትን አድርጎ ይሠራልን?
21ስለዚህ፥ እነሆ፥ አስታውቃቸዋለሁ፥ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፥ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 16: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ