መጽሐፈ መሳፍንት 7:15-23

መጽሐፈ መሳፍንት 7:15-23 አማ54

ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜውን በሰማ ጊዜ ሰገደ፥ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ፦ እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ አለ። ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮውም ውስጥ ችቦ ሰጠ። እርሱም፦ እኔን ተመልከቱ፥ እንዲሁም አድርጉ፥ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፥ እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ፦ ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን በሉ አላቸው። ጌዴዎንም ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት ትጋቱም በተጀመረ ጊዜ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፥ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፥ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮች ሰባበሩ። ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፥ ማሰሮችንም ሰበሩ፥ በግራ እጃቸውም ችቦችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ፦ የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ ብለው ጮኹ። ሁሉም በየቦታው በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፥ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፥ ጮኸ፥ ሸሸም። ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶች ነፉ፥ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራውና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፥ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሺጣ ድረስ በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልምሖላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ።