መጽሐፈ መሳፍንት 7
7
1ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፥ በሐሮድ ምንጭ አጠገብም ሰፈሩ፥ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
2እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፥ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም። 3አሁንም እንግዲህ፦ የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ አሥርም ሺህ ቀሩ።
4እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፥ ወደ ውኃ አውርዳቸው፥ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፥ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፥ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም አለው። 5ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፥ እንዲሁም ሊጠጣ በጉልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው አለው። 6በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቁጥር ሦስት መቶ ነበረ፥ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጉልበታቸው ተንበረከኩ። 7እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፦ በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፥ ምድያማውያንንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፥ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ አለው። 8የሕዝቡንም ስንቅና ቀንደ መለከት በእጃቸው ወሰዱ፥ የቀሩትንም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፥ ሦስቱን መቶ ሰዎች ግን በእርሱ ዘንድ ጠበቃቸው፥ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
9በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር፦ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና ተነሥተህ ወደ ሰፈር ውረድ። 10አንተም ለመውረድ ብትፈራ አንተ ከሎሌህ ከፉራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፥ 11የሚናገሩትንም ትሰማለህ፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትወርድ ዘንድ እጅህ ትበረታለች አለው። እርሱና ሎሌው ፉራ በሰፈሩ ዳርቻ ወደ ነበሩት ሰልፈኞች ወረዱ። 12ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ሰዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፥ የግመሎቻቸውም ብዛት ቁጥር እንደሌለው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ። 13ጌዴዎንም በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለባልንጀራው ሲያጫውት፦ እነሆ፥ ሕልም አለምሁ፥ እነሆም፥ አንዲት የገብስ እንጎቻ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ወረደች፥ ወደ ድንኳኑም ደርሳ እስኪወድቅ ድረስ መታችው፥ ገለበጠችውም፥ ድንኳኑም ተጋደመ ይል ነበር። 14ባልንጀራውም መልሶ፦ ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፥ እግዚአብሔር ምድያምንና ሠራዊቱን ሁሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል አለው።
15ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜውን በሰማ ጊዜ ሰገደ፥ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ፦ እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ አለ። 16ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮውም ውስጥ ችቦ ሰጠ። 17እርሱም፦ እኔን ተመልከቱ፥ እንዲሁም አድርጉ፥ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፥ 18እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ፦ ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን በሉ አላቸው።
19ጌዴዎንም ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት ትጋቱም በተጀመረ ጊዜ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፥ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፥ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮች ሰባበሩ። 20ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፥ ማሰሮችንም ሰበሩ፥ በግራ እጃቸውም ችቦችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ፦ የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ ብለው ጮኹ። 21ሁሉም በየቦታው በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፥ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፥ ጮኸ፥ ሸሸም። 22ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶች ነፉ፥ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራውና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፥ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሺጣ ድረስ በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልምሖላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። 23የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ።
24ጌዴዎንም፦ ምድያምን ለመገናኘት ውረዱ፥ እስከ ቤትባራም ድረስ ያለውን ውኃ፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙባቸው ብሎ መልክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ተራራማ አገር ሁሉ ሰደደ። የኤፍሬም ሰዎችም ሁሉ ተሰብስበው እስከ ቤትባራ ድረስ ውኃውን፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙ። 25የምድያምን ሁለቱን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን ያዙ፥ ሔሬብንም በሔሬብ ዓለት አጠገብ ገደሉት፥ ዜብንም በዜብ መጥመቂያ ላይ ገደሉት፥ ምድያምንም አሳደዱ፥ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ጌዴዎን መጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ