መጽሐፈ መሳፍንት 15:1-12

መጽሐፈ መሳፍንት 15:1-12 አማ54

ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና፦ ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፥ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው። አባትዋም፦ ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋት፥ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው። ሶምሶንም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው። ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፥ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች መካከል አንድ ችቦ አደረገ። ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፥ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ። ፍልስጥኤማውያንም፦ ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም፦ ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ። ሶምሶንም፦ እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው። እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፥ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ። ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች፦ በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም፦ ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ። ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን፦ ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም፦ እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው። እነርሱም፦ አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም፦ እናንተ እንዳትገሉኝ ማሉልኝ አላቸው።