ትንቢተ ኢሳይያስ 9
9
1ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፥ በኋለኛው ዘመን ግን የዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። 2በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፥ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። 3ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፥ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል። 4በምድያም ጊዜ እንደሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር ያስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል። 5የሚረግጡ የሠልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል። 6ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፥ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። 7ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 8ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፥ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። 9-10በትዕቢትና በልብ ኵራት፦ ጡቡ ወድቆአል፥ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሰራለን፥ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፥ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን የሚሉ በኤፍሬምና በሰማርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ያውቃሉ። 11ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ ተቋቋሚ ያስነሳበታል፥ 12ጠላቶቹም ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፥ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳን ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 13ሕዝቡ ግን ወደ ቀሰፋቸው አልተመለሱም፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም። 14ስለዚህ እግዚአብሔር እራስንና ጅራትን፥ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል። 15ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፥ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። 16ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፥ ተመሪዎቹም ይጠፋሉ። 17ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፥ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጕልማሶቻቸው ደስ አይለውም፥ ለደሃ አደጎቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 18ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፥ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፥ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፥ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል። 19በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ተቃጥላለች፥ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፥ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። 20ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል ይራብማል፥ በግራም በኩል ይበላል አይጠግብምም፥ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፥ 21ምናሴ ኤፍሬምን ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፥ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ