ትንቢተ ኢሳይያስ 48
48
1እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ 2በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ። 3የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል አሳይቼውማለሁ፥ ድንገት አድርጌዋለሁ ተፈጽሞማል። 4አንተ እልከኛ፥ አንገትህን የብረት ጅማት፥ ግንባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፥ 5ስለዚህ፥ አንተ፦ ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር ሳይሆንም አሳይቼህ ነበር። 6ሰምተሃል፥ ይህን ሁሉ ተመልከት፥ እናንተም የምትናገሩት አይደላችሁምን? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲሶች ነገሮችን ከዚህ ጀምሬ አሳይቼሃለሁ። 7እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፥ አንተም፦ እነሆ፥ አውቄአቸዋለሁ እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። 8አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፥ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደ ሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደ ተጠራህ አውቄአለሁና። 9ስለ ስሜ ቍጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳለጠፋህም ስለ ምሥጋናዬ እታገሣለሁ። 10እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፥ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። 11ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና፥ ክብሬን ለሌላ አልሰጥም። 12ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፥ እኔ ነኝ፥ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። 13እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፥ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። 14እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፥ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። 15እኔ እራሴ ተናግሬአለሁ፥ እኔ ጠርቼዋለሁ፥ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። 16ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፥ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፥ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። 17ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የሚመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። 18ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፥ 19ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። 20ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፥ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ ይህንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፦ እግዚአብሔር ባሪያውን ያዕቆብን ታድጎታል በሉ። 21በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፥ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። 22ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 48: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ