ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፥ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፥ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፥ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ። ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፥ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅንነት አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራው ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር፥ እኔ ነኝ። ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፥ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም፦ አይዞህ ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፥ ስለ ማጣበቅ ሥራውም፦ መልካም ነው አለ፥ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው። ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና፦ አንተ ባሪያዬ ነህ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፥ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፥ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል። የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፦ አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፥ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፥ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፥ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፥ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፥ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ።
ትንቢተ ኢሳይያስ 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች