ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-18

ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-18 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በደሴቶች የምትኖሩ ሕዝቦች! ጸጥ ብላችሁ አድምጡ! ሕዝቦች ኀይላቸውን ያድሱ፤ ወደ ፊትም ቀርበው ይናገሩ፤ በፍርድ ሸንጎ በአንድነት እንገናኝ። “ድል አድራጊውን አነሣሥቶ ከምሥራቅ ያመጣ፥ እንዲያገለግለው የጠራው ማነው? ሕዝቦችን አሳልፎ ለእርሱ ይሰጣቸዋል። ነገሥታትንም ያስገዛለታል፤ በሰይፉ እንደ ትቢያ በፍላጻዎቹም እንደ ገለባ ይበታትናቸዋል። ከዚህ በፊት እግሮቹ ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እነርሱን በፍጥነት ሲያሳድድ ምንም ጒዳት አይደርስበትም። ይህ እንዲሆን የፈቀደ ማን ነው? የታሪክንስ ሂደት የሚቈጣጠር ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ነበርኩ፤ በመጨረሻም የምገኝ እኔው ነኝ። “በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች እኔ ያደረግኹትን ሁሉ አይተዋል፤ ስለዚህም እጅግ ደንግጠው ተንቀጥቅጠዋል፤ በአንድነትም ተሰብስበው ወደ እኔ መጥተዋል። አንዱ ሌላውን ይረዳል፤ ወንድምም ወንድሙን ‘አይዞህ በርታ፤’ ይለዋል። የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤ ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም በመስፍ ላይ የሚመታውን ‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል። እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን በምስማር ይቸነክሩታል።” “ነገር ግን አንተ አገልጋዬ እስራኤል ሆይ! ሕዝቤ እንድትሆን የመረጥኩህ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ። ከምድር ዳርቻ አመጣሁህ፥ ከአራቱም ማእዘን ጠራሁህ፤ ‘አገልጋዬ ትሆናለህ’ ብዬ መረጥኩህ እንጂ አልጣልኩህም። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ። በአንተ ላይ የተቈጡ ሁሉ ተሸንፈው ያፍራሉ፤ አንተንም ለመጒዳት የሚነሡ ጠፍተው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ጠላቶችህን ትፈልጋቸዋለህ፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ በአንተ ላይ ጦርነት አስነሥተው የነበሩትም ፈጽሞ እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ‘አይዞህ አትፍራ፥ አትደንግጥ፥ ቀኝ እጅህን ይዤ እረዳሃለሁ’ እያልኩ የማበረታታህ፥ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ ትል ደካማ የሆንክ እስራኤል ሆይ! እኔ ስለምረዳህ አትፍራ፤ የምታደግህ የእስራኤል ቅዱስ እኔ ነኝ። እነሆ፥ እኔ እንደ ስለታም፥ አዲስና፥ ጥርስ እንዳለው የመውቂያ መሣሪያ አደርግሃለሁ፤ ተራራዎችንም በማበራየት ታደቃቸዋለህ፤ ኰረብቶችንም ዳምጠህ እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ። “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ አያገኙም፤ ጒሮሮአቸው ከጥማት የተነሣ ሲደርቅ፥ እኔ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እሰማለሁ፤ እኔም የእስራኤል አምላክ ከቶ አልተዋቸውም። በደረቁ ኰረብቶች ላይ ወንዞች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ በሸለቆዎችም ውስጥ የውሃ ምንጮች ያልፋሉ፤ በረሓዎችንም የኲሬ ውሃ መከማቻ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ደረቁም ምድር የምንጭ ውሃ መፍሰሻ ይሆናል።