የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:12-25

ትንቢተ ኢሳይያስ 40:12-25 አማ54

ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? የእግዚአብሔርም መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው? እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፥ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል። ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። አህዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፥ ከምናምን እንደሚያንሱ፥ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል። እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል። ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፥ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፥ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ አለቆችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። እንግዲህ እተካከላለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}