የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 28

28
1ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ! 2እነሆ፥ በጌታ ዘንድ ኃያል ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ታላቅ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል። 3-4የኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፥ በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፥ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል። 5በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፥ 6በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል። 7እነዚህ ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፥ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፥ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ። 8ማዕዱ ሁሉ ትፋትንና ርኩሰትን ተሞልቶአል፥ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም። 9እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? 10ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። 11በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፥ 12እርሱም፦ ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፥ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፥ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። 13ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል። 14ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 15እናንተም፦ ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፥ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ስላላችሁ፥ 16ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፥ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፥ የሚያምንም አያፍርም። 17ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፥ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። 18ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፥ የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። 19ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፥ ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል፥ ወሬውንም ማስተዋል ድንጋጤ ይሆናል። 20ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፥ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጎናጸፊያ ጠባብ ነው። 21እግዚአብሔርም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፥ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፥ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል። 22አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ። 23አድምጡ ድምፄንም ስሙ፥ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። 24በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይገለግላልን? 25ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃውንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን? 26ይህንም ብልሃት አምላኩ ያስታውቀዋል ያስተምረውማል። 27ጥቁሩ አዝሙድ በተሳለች ማሄጃ አያኬድም፥ የሰረገላም መንኮራኵር በካሙን ላይ አይዞርም፥ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። 28የእንጀራ እህል ይደቅቃልን? ለዘላለም አያኬደውም፥ የሰረገላውን መንኮራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም። 29ይህም ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊቱ ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ